የፍርድ ቤቱ ታሪክ

ኢትዮጰያ ዘመናዊ የፍትህና የዳኝነት ስርዓት ከመገንባቷ ብዙ ዓመታት አስቀድሞ የተለያዩ ባህላዊና ሀይማኖታዊ የፍትህ እና የዳኝነት ስርዓትን ስታራምድ ኖራለች፡፡ ይህ የዳኝነት ስርዓት ኢትዮጵያዊ ባህልን፣ ወግን ፣ አኗኗርንና እምነትን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ የዳኝነት ስርዓት ሲሆን ስርዓቱን የሚዘውሩት ደግሞ የሀገር ሸማግልዎችና የሀይማኖት አባቶች ነበሩ፡፡ ይህ ስርዓት ዘመናዊ የዳኝነት እና የፍትህ ተቋማት ለመገንባታቸው የራሱን አስተዋጽዖ ያበረከተ ሲሆን በፍትህ አሰጣጥ ደረጃም ለዘመናዊው የዳኝነትና የፍትህ አሰጣጥ ሂደት የራሱን አሻራ አሳርፏል፡፡

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በህገ- መንግስቱ የዳኝነት ስርዓትን ለመከወን ስልጣን ከተሰጣቸው ከሦስቱ የዳኝነት ተቋማት አንዱና ከፍተኛ መዝገብ የሚታይበት ፍርድ ቤት ነው፡፡ ይህ ፍርድ ቤት ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ከፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀጥሎ የሚገኝ ሲሆን ብዙ ችሎቶች፣ ዳኞች፣ ረዳት ዳኞች፣ ሬጅስትራርና የአስተዳደር ሰራተኞችን በውስጡ የያዘ የፍርድ ቤት አካል ነው፡፡

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤት መቋቋሚያ አዋጅ ከተቋቋመ ጀምሮ ጊዜውን የሚመጥን የፍትህና የዳኝነት ስርዓት ለመገንባት እየሰራ ይገኛል፡፡ ተቋሙ በተለይም የዳኝነት ስርዓቱ ግልፀኝነትን የተላበሰ፣ ፍትሐዊ፣ በዘር፣ በቀለምና በጎሳ አድልዖ የሌለበት ፍርድ ለመስጠት እንዲሁም በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ ተዓማኒ ሆኖ በመገኘት ህዝቡ በተቋሙ ላይ ያለውን እምነት ከፍ ለማድረግ ብሎም ህዝባዊ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፤ እየተደረገም ይገኛል፡፡

በተለይም ዘመናዊነት እና አለማቀፋዊ የፍትሐ ስርዓት እያደገና እየዘመነ ሲመጣ የእኛ ሀገር የዳኝት ስርዓትም እያደገና እየተለወጠ ሊመጣ ችሏል፡፡ ይህንንም ለመተግበር የፌደራል ፍርድ ቤቶች መቋቋሚያ አዋጃቸውን በተለያዬ ጊዜ እንዲያሻሽሉ አስገድዷቸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የፍርድ ቤት መቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 ፀድቆ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ በዚህም መሰረት በፊት ከነበረው ከብር 5001 (አምስት ሺህ አንድ ብር) ጀምሮ እስከ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) የስረ ነገር ስልጣን በተጨማሪ አስቀድሞ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታዩ የነበሩ የገንዘብ መጠናቸው እስከ ብር 10,000,000(አስር ሚሊዮን) የሚደርሱ የፍትሀብሄር ጉዳዮች እና በአዋጁ የተዘረዘሩ የወንጀል ጉዳዮች በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታዩ ተደንግጓል፡፡

የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ የሚታዩ የወንጀል ክሶችን በመመርመር ብይን ይሰጣል፡፡ ፍርድ ቤቱ የተለዬ ችሎት የሚታይባቸው ምድብ ችሎቶችን ማዘጋጀቱ እንዳለ ሆኖ ሁሉንም ወንጀሎች በሁሉም ምድብ ችሎቶች ይሰጣል፡፡ በተለይም ከፌደራል መንግስቱ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚነሱ ወንጀሎች የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እይታዎች ናቸው፡፡