መግቢያ

የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ካለው ቀልጣፋ፡ ተደራሽ እና ተአማኒነት ያለው ፍርድን በመስጠት ፍትህን ማስፈን አላማና እቅድ አንፃር የሚቀርቡለትን ጉዳዮች አከራክሮ ለመወሰን የሚያደርገው ከፍተኛ ቢሆንም በፍርድ ቤቶቹ ካለው የክስ ጉዳዮች ብዛትና መዝገቦች ፍሰት አንፃር የፍርድ ቤት ጉዳዮችን በመደበኛው የክርክር ሂደት ብቻ በመከተል የፍርድ ቤቱን ተጠቃሽ አላማዎች ለመፈፀም ከመደበኛ የፍርድ ቤት ክርክር ሂደት (litigation system) ውጪ ያሉ አማራጭ ክርክር መፍቻ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በፍርድ ቤት ማሻሻያ እቅድ አፈፃፀም የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት (court annexed mediation) ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎትን እንደ አንድ የፍትህ ዓምድ አድርጎ በመውሰድ በፍርድ ቤት መደበኛ የክርክር ሂደት የሚስተዋለውን የመዘገብ መብዛት፡ የስራ መደራረብ እና ጉዳዮች የሚፈጁትን የጊዜ ርዝመት፡ የሚያስከትለው ወጪ እንዲሁም ከተከራካሪ ወገኖች ዘላቂ ግንኙት አንፃር ታሳቢ በማድረግ ለፍርድ ቤት የቀረበ የክርክርን ጉዳይ በፍርድ ቤቱ ስር በስራ ክፍልነት በተቋቋመው የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት እንዲመራ እና እንዲታይ በማድረግ ላይ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ይገልፃል፡፡

የማስማማት አገልግሎት ባለድርሻ አካላት ማናቸው? ኃላፊነታቸውስ ምንድነው?

 • አስማሚ ባለሙያዎች ማንናቸው? የፍርድ ቤቱ አስማሚዎች፡
 1. ረዳት ዳኖች፡ የፍርድ ቤቱ አስማሚዎች የሚባሉት በዋናነት በማስታረቅ መስክ ተጨማሪ ስልጠና የወሰዱ ረዳት ዳኞች ሲሆኑ እነዚህ ረዳት ዳኛ አስማሚዎች እንደ ዳኝነት ስልጣን ሳይሆን እንደ አስማሚ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡
 2. ከእነዚህ የህግ ባለሙያዎች ጋራ በመሆን እንዲሁ በዘርፉ ስልጠና የወሰዱ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች፡ በፍ/ቤቱ ያሉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎች በተለይም በፍቺ ችሎት ማስማማት ላይ የህፃናት መብትና ጥቅም በአግባቡ እንዲጠበቅ፡ ለፍቺ የቀረቡትን ተጋቢዎች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የማረጋገት፡ ክብካቤ የማድረግ እና የማስተማር እንዲሁም በልጅ አስተዳደግ ላይ የእርቅ መንፈስን ባለቀቀ መልኩ ሙያዊ እገዛዎችን ያደርጋሉ፡፡
 • ከፍ/ቤቱ ውጪ የሚመጡ ስልጠና እና የስራ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች ናቸው፡፡ እነዚህም የዩኒቨርሲቲ አስተማሪዎች፡ በህፃናት ጉዳይ ላይ ልዩ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች፡ ጡረታ የወጡ ዳኞች እንዲሁም በስራ ላይ ያሉ ጠበቆች ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ባካበቱት ሙያዊ ልምዳቸው ታግዘውና ከላይ ከተመለከቱት የፍ/ቤቱ አስታራቂዎች ጋር በመቀናጀት የማስማማት ስራ ይወጣሉ፡፡
 • የመዝገቡ ተከራካሪ ወገኖች፡ ለአስታራቂዎች በሚመራው መዝገብ ውስጥ ያሉ ተከራካሪ ወገኞች ማለትም ከሳሽ እና ተከሳሽ በማስታረቅ አገልግሎት ውስጥ ዋነኞቹ አካላት ናቸው፡፡
 • ፍርድ ቤት ወይም ችሎቱ፡ የፍ/ቤቱ ችሎት ክስ በቀረበ ጊዜ ጉዳዩ ወደ አስታራቂ በመምራት ቀጠሮ እንዲይዝ ማድረግ፡ የማስታረቅ ሂደቱ ቀጥሎም ግራቀኙ ስምምነት ላይ የስምምነት ሰነድ ለፍርድ ቤቱ በቀረበ ጊዜ የፍትሐብሔር ሥነ ስርዓት ህጉ መሰረት ግራቀኙ በነፃ ፈቃዳቸው መስማማታቸውን በማረጋገጥ የስምምነት ሰነድ ተቀብሎ በማዕደቅ መዝገቡን መዝጋት የፍርድ ቤቱ ድርሻ ነው፡፡

የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት ማለት ምንድነው?

የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት፡ (court annexed mediation)፡ ማለት በፍ/ቤት ችሎት በሚመራ በአንድ የፍ/ቤት አስማሚ ወይም በፍ/ቤት ስር በዚሁ የማስማማት መስክ ከሚመለከተው አካል በቂ ስልጠና በመውሰድ እውቅና የተሰጠው አካል በፍርድ ቤት ለቀረበ ክስ ወይም ክርክር ተከራካሪ አካላትን በጋራ በማቀራረብ አንድ የመፍትሔ ሃሳብ ላይ እንዲደርሱ፡ የሚያነጋግር፡ በመካከላቸው ውይይት እንዲኖር የሚያደርግ፡ ያላቸውን ልዩነት ወይም የጉዳዩን ጭብጥ ግራቀኙ እንዲለዩና እንዲያውቁት በጋራ የሚሰራ፡ ግራቀኙ ሊደራደሩባቸው የሚችሉ ጉዳዮችን ወይም ነጥቦችን ግራ ቀኙ ከሚደርሱበት የአንድነት ሃሳብ በመነሳት የመደራደሪያ ነጥቦችና የድርድር ይዘቶችን ለተከራካሪ አካላት በማቅረብ የሚሰራ እንዲሁም የቀረበውን ጉዳይ በእርቅ ለመጨረስ  የግራቀኙን ልዩነቶች ለማጥበብ እንዲቻል የመፍትሔ ሃሳቦችን የሚያቀርብ  የማቀራረብና የማስማማት ስራ በሚሰራ ባለሙያ አጋርነትና አደራዳሪነት የሚደረግ በነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ፤ በፍርድ ቤት በተቋቋሙ የማስታረቅ አገልግሎት ቢሮዎች ውስጥ የሚደረግ የስምምነት ሂደት ነው፡፡

የፍርድ ቤት መር አስማሚ የማስማማት አገልግሎት ለተገልጋዩ ምን ጥቅም ይሰጣል?

 • ና ነፃነት፡ በነፃ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ፡ የፍርድ ቤት መር የማስታረቅ አገልግሎት በፍ/ቤቱ አስታራቂ ቢሮ ውስጥ ግራ ቀኙ ባለጉዳዮች ብቻ በተገኙበት፡ እንደ መደበኛው ክርክር በችሎት የማይደረግ በመሆኑ ተስማሚዎች በነፃነት ሃሳባቸው እንዲገልጹ እና እንዲነጋገሩ ከችሎት ይልቅ ትልቅ ሃሳባቸውን የመግለፅ ነፃነት ይሠጣል፡፡
 • ጊዜ እና የገንዘብ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል፡
 • የተጣፋጠነ ፍትህን ለመስጠት ይረዳል፡
 • አገልግሎቱ በመመሪያ በተለየ ሁኔታ እስከሚደነገግ ድረስ በነፃ እየተሰጠ ያለ አገልግሎት መሆኑ፡ ተገልጋዮች ያለ ምንም ክፍያ የሚስተናገዱ ሲሆን በመደበኛው ክርክር ያሉ ወጪዎችን ጠበቃ መቅጠርን ጨምሮ ለመሸፈን የማይችሉ ወገኖችም በዚህ የማስታረቂያ አገልገሎት በፍ/ቤቱ ረዳት ዳኖችና ስልጠና በወሰዱ አከካላት በነፃ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ይህም የፍትህ ተደራሽነትን እውን ያደርጋል፡፡
 • በአስታራቂ አገልግሎት ሁሉም አሸናፊ ናቸው፡ በዚህ አገልግሎት ግራቀኙ ተከራካሪ የሆኑ ወገኞች ሁለቱም በጉዳዩ አሸናፊ ይሆናሉ፡፡ በማስታረቅ ሂደት ግራቀኙ በክርክሩ የራሳቸው ጉዳይ ዳኛ በመሆናቸው፡ ሁለቱንም የሚያስማማ ውሳኔ የሚያሣልፉ በመሆኑ ሁለቱም ወገኖች አሸናፊ ናቸው፡፡ በመደበኛው ክርክር ሁሌም አንድ አሸናፊ ነው፡፡
 • የግራቀኙን ዘላቂ መልካም ግንኙነት የሚያሰፍንና የሚያስቀጥል መሆኑ፡ በማስታረቅ የሚቋጭ ክርክር በተስማሚዎቹ መካከል ያለውን ወይም የነበረውን መልካም ግንኙነት የሚያስቀጥል ነው፡፡

ከመደበኛው የፍርድ ቤት ክርክር ምን ይለየዋል?

 • በግራቀኙ ተከራካሪ ወገኖች ነፃ ፈቃድና ስምምነት ብቻ ላይ መሰረት ያደርጋል፡፡
 • ግራቀኙ በሚያስማማቸው ማናቸውም ነጥቦች ላይ በፈለጉበት አግባብ ተስማምተው ክርክራቸውን በስምምነት ማስቀረት ይችላሉ፡፡ የፍ/ቤት ክርክር የመፍትሔ ምህዳሩ ጠባብ ነው፡፡ በፍ/ቤት የተሰጠን ውሳኔ ማስፈፀም የማይቻልባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡
 • አጭር ጊዜ የሚወስድ ነው እንዲሁም በጣም በአጫጭር ቀጠሮች በድጋሜ መቅረብ ይቻላል፡፡ የማሰቢያ ጊዜን የማይነፍግ ነው፡፡
 • አስማሚው የዳኝነት ስልጣንን የማይጠቀም መሆኑ፡፡ የትኛውም አካል ዳኛ ሆኖ ቢቀርብ ስራው ግራቀኙን ማቀራረብና ማስማማት ነው፡፡
 • የውሳኔው መሰረት መነጋገር፡ መግባባትና መወሰን የተስማሚዎቹ ወይም የተከራካሪ ወገኖቹ የዳኝነት ስልጣን መሆኑ
 • የሥነ ስርዓት ህጉን የክርክርና ማስረጃ አቀራረብ አይከተልም፡፡ በሥነ ሥርዓት ህጉ ያለውን ጊዜ የሚፈጅ የክርክር ሂደትና ማስረጃ አቀራረብ የማይከተል በመሆኑ ምቹና ቀላል ነው፡፡

 

የማስማማት አገልግሎቱ መቼ ይሰጣል?

በፍርድ ቤት የማስማማት አገልግሎት በመዝገቡ እንደ መልስ መቀባበልና ክስ መስማት ቀጠሮ የሚሰጠው ሲሆን ይህም ቀጠሮው በመልስ መቀባበልና ክስ መስማት መሃል የክስ መስማቱ ሂደት ከመሰማቱ በፊት ባለው አንድ ቀን ይሆናል፡፡ በአንድ ቀን ቀጠሮ የማያልቅ  ከሆነ አስታራቂዎቹ ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጡ ይሆናል፡፡ ለቤተሰብ ችሎት የፍቺ ጉዳዮች በመጀመሪያው ቀጠሮ ካልተስማሙ ሁለተኛ ቀጠሮ የማሰላሰያ ጊዜ በችሎት በተሰጠበት ጊዜ በድጋሜ ሊቀጠር ይችላል፡፡

የትና ምን ምን ጉዳዮች በአስታራቂ በኩል ይታያሉ?

የማስማማት አገልግሎት በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ እንዲሰጥ በአዋጅ የተደነገገ ሲሆን ስራውን ለማስጀመርና ለማስፋፋት አሁን በአምስት ምድብ ችሎቶች በሶስት የክስ አይነቶች ለመስራት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ይኸውም

 • በልደታ ምድብ ችሎት፡ የቤተሰብ ችሎት አና ንግድ ችሎት
 • በቂርቆስ ምድብ ችሎት፡ የቤተሰብና ስራ ክርክር ችሎት
 • በቦሌ ምድብ ችሎት፡ የቤተሰብና ስራ ክርክር ችሎት
 • በየካ ምድብ ችሎት፡ የቤተሰብና ስራ ክርክር ችሎት
 • በመናገሻ ምድብ ችሎት፡ የቤተሰብና ስራ ክርክር ችሎት አገልግሎቱ የሚሰጥ ይሆናል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥናት በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተመለከቱት ጉዳዮች መልካም እምርታዎች እየታዩ ሲሆን በ2012ዓ/ም የአገልግሎቱ አፈፃፀም 74% ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በዚህም በጀት አመት በአምስት ወራት ውስጥ እንኳ ከ100 በላይ የፍርድ ቤት ክርክር መዝገቦች በስምምነት እንዲቋጩ ሆኗል፡፡

 

ለዚህ የፍርድ ቤት ማስማማት አገልግሎት ማስተዋወቅ ስራ የተመረጡ ጉዳዮችና ሂደታቸው

 • የጉዳዩ አይነት፡- የስራ ክርክር ጉዳይ ሲሆን በዚህም የችሎት ጉዳይ 25 ሰዎች በአንድ ድርጅት ላይ በመዝገብ ቁጥር 163509 ክስ ያቀረቡ ሲሆን እነዚህ ሰራተኞች ከአሰሪው ድርጅት ጋር ያላቸውን አለመግባባት ወደ ስምምነት እንዲደረግ እና በፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት ስር እንዲታይ በዳኛ ከተመራ በኋላ ወደ አስማሚው ተመርተው የማስማማት ስራ ተሰርቶላቸው በመጨረሻም ስምምነት ላይ ደርሰው ክርክሩን በስምምነት መጨረስ ተችሏል፡፡ የክርክሩም ይዘት ከሳሽ ሰራተኞች ተከሳሽ የስራ ለውጥ በማድረግ ላደረገው ስንብት የከፈለው ካሳ አነስተኛ በመሆኑ ስንብቱ ህገ ወጥ ነው እንዲባልና ክፍያዎች እንዲከፈላቸው የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁን ጠቅሰው ክስ አቅርበዋል፡፡ ተከሳሽም ስራውን ለማዘመን ስራውን በዘርፉ ልምድ ላለው የውጪ አካል አስተላልፌአለሁ(outsource) አድርጌአለሁና አውትሶርስ ማድረግ ለስንብት በቂ ምክንያት እንደሆነ በመጥቀስ ክርክር አቅርቧል፡፡ በዚህ ደረጃ ግራቀኙ ክርክር ያቀረቡ ሲሆን ጉዳዩ ወደ አስማሚ ተመርቶ ጉዳዩ የታየ ሲሆን በአስማሚው ከፍተኛ ሚና እና በግራቀኙ ጉዳዩን ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ በመሆኑም ጭምር ስንብቱ እንደፀና ሆኖ ተጨማሪ ክፍያ ላይ ድርድር ተደርጎ ክፍያ እንዲጨመር ተስማምተዋል፡፡

የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት የህግ ማዕቀፍ፡

በፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በተጠቀሱት የጉዳይ አይነቶች ላይ የማስማማት ስራ ሲተገብር የቆየ ሲሆን ለዚህ ስራ የፍርድ ቤት ማሻሻያነት በፌደራል ፍርድ ቤቶች አመራር የተወሰነ መሆን እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ስነ ስርዓት ህግ አንቀፅ 274 ለፍርድ ቤት የቀረቡ ጉዳዮች በስምምነት መቋጨት እንደሚችሉ ህግ በመደንገጉ ሲሆን ከዚህ በኋላ በኢፌድሪ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በፀደቀው የፌደራል ፍርድ ቤቶች ስልጣና ማሻሻያ አዋጅ መሰረት በአዋጅ የፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት የተቋቋመ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህም መሰረት አገልግሎቱ የአዋጅ ሆነ የስነ ስርኣት ህግ ድጋፍ ያለው ነው፡፡

 • በማስማማት ሂደቱ ተካፋይ አካላት፡-
 1. የስራ ክርክር ችሎቱ ዳኛ፡- ክስ ሲቀርብ በመዝገቡ ቀጠሮ ይሰጣል፡፡ ቀጠሮውም በቅድሚያ ከሳሾች ባቀረቡት ክስ ላይ ተከሳሽ መልስ እንዲሰጥ አንድ ቀጠሮ፡ ከዚያም በኋላ ጉዳዩ ክስ በችሎት ከመሰማቱ በፊት ወደ አስማሚ እንዲሄድና ግራ ቀኙ አስማሚው ዘንድ ቀርበው የማስማማት ሂደቱ እንዲቀጥል ያደርጋል፡፡
 2. ሬጂስትራር፡- ዳኛው በሰጠው አግባብ ለተከሳሽ መጥሪያ እንዲደርስና በደረሰው መጥሪያ መሰረት ተከሳሽ የፅሁፍ መከላከያ መልሱን ይዞ በሚቀርብ ጊዜ መልስ ማለዋወጥና መዝገቡ በቀጣይነት ወደ አስማሚ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡
 3. የፍርድ ቤት መር አስማሚ፡- አስማሚው ግራቀኙ አስማሚ ማዕከል እንዲቀርቡ በዳኛ በተሰጣቸው ትዕዛዝ መሰረት መቅረባቸውን ተጠባብቆ የማስማማት ሂደቱን እና ጥቅሙን ለግራቀኙ ተስማሚ አካላት ገለፃ በማድረግ የማስማማት ሂደቱን በመክፈት ሂደቱን ተከትሎ ግራቀኙ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ሙያዊ ድጋፍና ጥረት በማድረግ ስምምነት እንዲደርሱ ያደርጋል፡፡ ጉዳዩም በግራቀኙ ስምምነት ከተጠናቀቀ በኋላ ስምምነቱን ወደ ፅሑፍ የስምምነት ውል በመለወጥና በማድረግ ከመዝገቡ ጋር የስምምነት ሰነዱን ወደ ችሎቱ ዳኛ ይልካል፡፡
 4. የችሎቱ ዳኛ፡- በመዝገቡ የተሰየመው የችሎት ዳኛ ወደ ስምምነት የተላከውን መዝገብ የስምምነት ውል በመመርመር እና በማጣራት በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ህግ አንቀፅ 277 መሰረት የስምምነት ውሉ ከህግና ከሞራል የማይቃረን መሆኑን በማጣራት የስምምነት ሰነዱን ተቀብሎ ያፀድቃል፡፡ የፀደቀው የስምምነት ውል እንደ ማንኛውም የፍርድ ቤት ውሳኔ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡
 5. የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች፡ ፍርድ ቤቱ ይህን አገልግሎት ማስጀመር የፈለገበትን አላማ ገለፃ እንዲያደርጉ

ልብ ይበሉ፡- ወደ ፍርድ ቤት መር ማስማማት አገልግሎት የተመራ መዝገብ ላይ መስማማት ግዴታ ባይሆንም በተሰጠው የማስማማት አገልግሎት አለመቅረብ በአዋጁ መሰረት በማስማማት ቀጠሮው ላይ ያልቀረበ ወገን ለቀረበው ወገን የወጪ ኪሳራ ካሳ እንዲከፍል ተደርጎ ጉዳዩ በችሎት እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡