የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለዳኞች፣ ለሬጅስትራሮች፣ ቡድን መሪዎች፣ የስራ ክፍል ሀላፊዎች እና ባለሙያዎች ከሰኔ 0 7/2016 ዓ.ም ጀምሮ ለ3 ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ አዱላላ ሪዞርት በችሎት አመራር እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ስልጠና እና ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዘዳንት ክብርት ወ/ሮ አሸነፈች አበበ ሲሆኑ በመክፈቻ ንግግራቸው በብዙ መለኪያ ሲታይ የፍርድ ቤቱ የመፈጸም አቅም ያደገ መሆኑን ፣ የፍርድ ቤቱ የ9 ወራት የመዝገብ አፈጻጸም 113% መሆኑን ፣ የፍርድ ቤት መር አስማሚነት በተመለከተ ከ 800 መዛግብት በላይ በ 10 ወሩ በእርቅ መቋጨታቸውን፣ የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያ መሠረት 93.7 % የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ መሠራቱን፣ የዳኞች የ 2015 አፈፃፀም ምዘና መከናወኑን እንዲሁም የ 2016 ምዘና ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ መሆኑን ፣ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መስራት እንዲሁም ምቹ የስራ አካባቢን ከመፍጠር አኳያ በቦሌ፣ ለሚ ኩራ መሰራቱን በቀጣይ ወደ ኮልፌ አዲስ ህንፃ ዝውውር እንደሚደረግና የዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በንግግራቸው የተገለጸ ሲሆን የሚታዩ ውስን የስነ ምግባር ችግሮችን ቀርፎ የህዝብ አመኔታን ያተረፈ ፍርድ ቤት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆን እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት በችሎት አመራር እና በአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ላይ ያተኮረ ሲሆን የችሎት አመራርን በሚመለከት ስልጠና የሰጡት የፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ክቡር አቶ ፉአድ ኪያር ሲሆኑ ፍርድ ቤቱ የህዝብ አመኔታን ያተረፈ የዳኝነት ተቋም ይሆን ዘንድ በስነ ምግባር መስራት ፣ ሁሉም የፍርድ ቤቱ ማህበረሰብ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት እና ተቋማዊ ባህልን መገንባት እንደሚያስፈልግ ይህን ለመተግበር የችሎት ሥርዓት መመሪያን በጥብቅ መተግበር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡