በድህረ-ውሳኔ መዛግብት ምርመራ እና በ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሁሉም ዳኞች ጋር ውይይት ተደረገ።
/ Categories: News

በድህረ-ውሳኔ መዛግብት ምርመራ እና በ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ከፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሁሉም ዳኞች ጋር ውይይት ተደረገ።

በድህረ-ውሳኔ መዛግብት ምርመራ እና በ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም ሪፖርት ላይ ሁሉም የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች በተገኙበት ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም በካፒታል አዲስ አበባ ሆቴል ውይይት ተደረገ።

በመርሃ ግብሩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ፋአድ ኪያር ፍርድ ቤቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ያስጠናውን "የድህረ ውሳኔ መዛግብት ምርመራ" ሪፖርት ሰነድን አስመልክቶ በተናገሩበት ወቅት ባለፋት አምስት የስትራቴጂክ ዕቅድ ዓመታት በውስንነት ከተለዮት ችግሮች አንዱ የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት መሆኑን በማስታወስ ፍርድ ቤቱ በ2018 በዕቅድ ከያዛቸው ስራዎች አንዱ የድህረ ውሳኔ መዛግብት ምርመራ ማከናወን መሆኑን አስገንዝበዋል።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸዉ የዳኝነት አገልግሎት ጥራትን ከሚያረጋግጡ ቁልፍ መሳሪያዎች አንዱ ተከታታይነት ያለው የድህረ-ውሣኔ ኦዲት ስራ መስራት መሆኑን በመግለፅ በተለይም ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ወጥነት ያለው አሠራርን ለማስፈን፣ የስልጠና ፍላጎትን ለመለየት፣ ተጠያቂነት እና ግልፅነት ለማስፈን፣ ክፍተቶችን ለይቶ ለማስተካከል እና የሕዝብ አመኔታ ለማግኘት የድህረ-ኦዲት ውሣኔ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ክቡር ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው የድህረ ውሳኔ ምርመራው አላማ 1ኛ. የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥ ከመዝገብ መክፈት ጀምሮ መዝገቡ በፍርድ፣ በዉሳኔ፣ በብይን ወይም በትእዛዝ እስኪዘጋ ድረስ ያለዉ ሂደት የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን እና መሰረታዊ ሕጎችን መሠረት በማድረግ የተሰጠ መሆኑን ለማረጋገጥ እና ክፍተቶች ካሉም ክፍተቶቹን ለመለየት፤ በተጨማሪም የጥራት ደረጃን፣ ተገማችነትን፣ ወጥነትን እና ፍትሃዊ የዳኝነት አሰጣጥ ለማረጋገጥ / ለማጠንከር 2ኛ. የመዝገብ ምርመራ ዉጤቱን መሰረት በማድረግ የፈጻሚዉን የብቃት ደረጃ በመመዘን በስልጠና ሊስተካከሉ የሚችሉ ክፍተቶችን በስልጠና ለሙሙላት እንዲሁም በአስተዳደራዊ እርምጃ ሊፈቱ የሚችሉ ክፍተቶችን በፍርድ ቤቱ አስተዳደር በኩል እንዲፈቱ ለማድረግ እንዲሁም 3ኛ በመዝገብ ኦዲት ምርመራዉ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ጥሰት የተፈፀመ መሆኑን የሚያሳዩ ግኝቶች ከተገኙ በፈፃሚዉ ላይ የሥነ-ምግባር ክስ በማቅረብ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ ቀልጣፋ፣ ተገማች እና ዉጤታማ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት ተገልጋዩ ማኅበረሰብ በፍርድ ቤቱ ላይ ያለዉ አመኔታ እንዲጨምር ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።

በመቀጠል የድህረ -ውሳኔ መዛግብት ምርመራ ኦዲትን አስመልክቶ የጥናቱ ግኝት ሪፖርቱ በዝርዝር ጥናቱን ባደረጉት የኮሚቴው ሰብሳቢ ዳኛ ዳንኤል አበበ እና በኮሚቴው አባል ዳኛ ዳንኤል ዱጋሳ ቀርቧል።

በመርሃ-ግብሩ በቀጣይ የቀረበው የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ሲሆን ከመዝገብ አፈፃፀም፣ ቅድሚያ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እንዲሁም ከፍትሃብሄር ጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር መመሪያን በጥብቅ ከመተግበር በተለይም ከጊዜ ገደብ በተጨማሪ ግልፅ ችሎት ከማስተናገድ፣ ቅድሚያ ትኩረት ከሚሹ ተገልጋዮች (ነፍሰጡር፣ ህፃናት፣ አረጋዉያን ወዘተ እንዲሁም የስነ-ምግባር፣ የክትትል እና ድጋፍ፣ የአስማሚነት ስራ፣ የሬጅስትራር አገልግሎት አሰጣጥ፣ የባለሙያዎች አቅም ከመገንባት እና ከቅንጅታዊ ስራዎች ... ወ.ዘ.ተ አንፃር በርካታ የዳኝነት እና አስተዳደራዊ ተግባራት በዉስን የሰዉ ሀይል እና በጀት መከናወኑ ተገልፆል ።

በቀረበዉ ሪፓርት በጥንካሬ በ2018 በጀት ዓመት 116,931 መዝገቦችን ለመስራት ታቅዶ ለ143,931 መዝገቦች እልባት መሰጠቱ፡፡ ይህም በዕቅድ ለመስራት ከተያዘው መዛግብት አንፃር የፍርድ ቤቱ አፈፃፀም 123% መድረሱ በዚህም የማጥራት ምጣኔ 98.4% እና የባክሎግ ክምችት 0.2% መሆኑን ከዚህም በፍርድ ቤቱ ካለው የመዝገብ ፍሰት አንፃር ባልተጣጣመ የሰው ሀይል እና የበጀት ሁኔታ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡ ተገልጿል። እንዲሁም የፍርድ ቤት መር አስማሚነትን ከመተግበር አንፃር 5,076 ከቀረቡ መዝገቦች ውስጥ በበጀት ዓመቱ 1,630 ጉዳዮች በስምምነት እንዲያልቁ መደረጉ ይህም የእቅዱን 30% መሆኑ ፣ የዳኞች ሰራ አፈፃፀም ጊዜውን ጠብቆ ለ3ኛ ጊዜ መደረጉ እና የ2017 ዓ.ም ምዘና ተካሄዶ የላቀ አፈፃፀም ያላቸውን የመሸለም እንዲሁም ለዳኞች የምዘና ዉጤታቸውን በአካል የማሳወቅ ስራ መሰራቱ ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱ፣ አመራሩ በሁሉም ምድብ ችሎቶች ወርዶ ድጋፍ እና ክትትል ማድረጉ፣ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የተሰሩ ተግባራት፣ የድህረ ፍርድ (ዉሳኔ) በከፊል ምድብ ችሎቶች መከናወኑ፣ የስነምግባር ክትትል ተጠያቂነት ስርዓት የማጠናከር፣ ከይግባኝ የሚመለሱ መዛግብት ክትትል፣ የቅድሚያ አገልግሎት ስርዓት... ወ.ዘ.ተ በስኬት የተመዘገቡ መሆናቸው እና ለተመዘገበው ውጤትም የፍርድ ቤቱ አመራሮች፣ ክቡራን ተጠሪ ዳኞች፣ ዳኞች፣ ዳይሬክተሮች፣ የጉባኤ ተሻሚዎች እና የፍርድ ቤቱ ሰራተኞች የነበራቸው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገልፆል።

በተቃራኒዉ የ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ እቅድ አፈፃፀም ግምገማ እንዲሁም በተገልጋይ እርካታ ጥናት በድክመት የተለዮ ከስነ-ምግባር አንፃር በተለይም ለችሎት ቅርበት ካላቸው አስተዳደር ሰራተኞች ጋር በጎላ፣ በዳኝነት አገልግሎት ጥራት፣ ተገማች ውሳኔ ከመስጠት፣ የዘገዮ መዛግብት ከማጥራት፣ ልዮ ድጋፍ ለሚሹ ቅድሚያ መስጠት ጋር በተያያዘ የተለዮ ችግሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶባቸው ሊሰራ እንደሚገባ መግባባት ተደርሷል::

በቀረቡት ሁለት ሪፖርቶች ላይ ከተሳታፊዎች አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ቀርበው ውይይት የተደረገ ሲሆን በሚመለከታቸው ኃላፊዎች እና የጥናቱ አቅራቢ አባላት ምላሾች የተሰጡ ሲሆን በፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፉዓድ ኪያር የዳኝነት አገልግሎቱን አሁን ካለበት የተሻለ ለማድረግ እና የስራ አፈፃፀም አጠናክሮ ለመቀጠል እንዳለበት በማጠቃለል እና በመግባባት ስብሰባው ተጠናቋል።

Previous Article አዲስ ለተሾሙ ረዳት ዳኞች የትውውቅ እና የስልጠና መርሃ-ግብር ተዘጋጀ።
Next Article በመድን ሽፋን (Insurance Coverage ) ህግ እና አሰራር ላይ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።
Print
421